የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ጥራት ለማሻሻል እና ወደ ኤሌክትሪክ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

 የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሃሰን ቀደም ሲል በነዳጅ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫዎች ላይ ይስተዋል የነበረውን የጥራት ማነስ እና ህገወጥ አሠራር ለመቅረፍ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታወቁ።
 
ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ የዘርፉ አቅርቦት ከዚህ ቀደም ጥራት የጎደለው፣ ለሐሰተኛ ምርቶች  የተጋለጠ እና ለተለያዩ ማጭበርበሮች ክፍት ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ጠንካራ የአቅርቦት ሰንሰለት ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
 
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪና የመለዋወጫ አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሽያጭ ማዕከላትንና የማገጣጠሚያ ተቋማትን እንዲመሠርቱ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
 
ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ፣ ሃይብሪድ እና የተፈጥሮ ጋዝ ለመቀየር የሚያስችሉ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የፖሊሲ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
 
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ አምራቾች፣ ተሽከርካሪ ገጣሚዎችና አከፋፋዮች የፋይናንስ አቅም እንዲጠናከር እና ጥራቱን የጠበቀ አሠራር እንዲከተሉ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
 
የከተማ እና የሀገር አቋራጭ ታክሲዎችን ወደ ኤሌክትሪክና ሌሎች ጽዱ የኃይል አማራጮች ለማሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል።
 
አቤል እስጢፋኖስ
 
ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *