በአዲስ አበባ ከተማ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና በተደራጀ መልኩ የሚፈጸሙ ‹‹የሀሰት እገታ›› ድርጊቶች በፖሊስ ስራ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታዉቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኘነት ሀላፊ ኮማንደር ቶማስ ጌታቸው፤አንዳንድ ግለሰቦች ለገንዘብ ጥቅም ሲሉ ‹‹ታግተናል›› በማለት ለቤተሰቦቻቸውና ለፖሊስ የሀሰት መረጃ በመስጠት ትልቅ የጸጥታ ስጋት ሲፈጥሩ ተስተውሏል ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች ህዝቡን ለማሸበርና በፖሊስ ላይ ያለውን እምነት ለመቀነስ ሆን ተብለው የሚዘጋጁ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ለገንዘብ ጥቅም ሲባል የሚፈጸሙ የሀሰት እገታ ድርጊቶችን ፖሊስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርመራ በማድረግ እውነታውን እያጋለጠና በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል፡፡
ስለሆነም ህብረተሰቡ መረጃዎችን ከተረጋገጡ የፖሊስና የመንግስት የመረጃ ምንጮች ብቻ እንዲያገኝ አሳስቧል።
በመጨረሻም ፖሊስ በቀጣይ የሚከበሩትን የመስቀልና የኢሬቻ በዓላትን በሰላም ለማክበር ከወዲሁ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ስራ መግባቱንና ህዝቡ እንደተለመደው ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
