“‘ፍቅር ያዘኝ… በፍቅር ተቃጠልኩ’ የሚለው ወግ በዛ ብሎልዎታል? አንዳንዴ ደግሞ ‘ሰው ሁሉ ያፍቅራል፤ እኔ ግን ምነው ፍቅር የሚባል ነገር ጨርሶ አይይዘኝም?’ ብለው ደንግጠው ያውቃሉ?
አይደንግጡ! በፍቅር አለመያዝዎ የግድ የጤና ወይም የስነ-ልቦና ችግር ላይሆን ይችላል ይሉናል ባለሙያው።
የስነ-አዕምሮና የስነ-ልቦና ባለሙያው እንዲሁም ደራሲ ዶክተር ኤልያስ ገብሩ ከኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ጋር ባደረጉት ቁይታ እንደገለጹት፤ አንዳንዶቻችን በቀላሉ ‘አሁን ጊዜው አይደለም’ ብለን ራሳችንን በፍቅር ከመያዝ ልንቆጥብ እንችላለን ይላሉ።
በስነ-ልቦናው ዓለም በፍቅር የመያዝ ስሜቱ ጨርሶ የሌላቸው ሰዎች ‘አሮማንቲክ’ ይባላሉ። እናም ባለሙያው እንደሚሉት፤ እነዚህ ሰዎች ስሜቱ ስለራቃቸው ብቻ ‘ታመዋል’ ማለት አይደለም።
ነገር ግን ነገሩ ሁልጊዜ እንዲህ ቀላል እና የተለመደ ላይሆን ይችላል ፡፡ ዶክተር ኤልያስ እንደሚሉት፤ በፍቅር የመያዝ አቅማችን ከልጅነት አስተዳደጋችንና ካለፈው የህይወት ተሞክሯችን ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው።
ወላጆቻቸው በፍቅርና በትዳር ህይወታቸው ጥሩ አርአያ ያልሆኑላቸው ወይም ፍቅር ሳይሰጣቸው ያደጉ ልጆች… ‘እኔ እኮ ፍቅር አይገባኝም’ የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ባይ ናቸው።
ደግሞም ከዚህ ቀደም አምነው ተጎድተው ወይም አፍቅረው ያጡ ሰዎችም ቢሆኑ… አዲስ የፍቅር ስሜት ለማስተናገድ ልባቸው ይፈራል፤ ይቸገራልም።
ወይም ደግሞ… ሙሉ በሙሉ በፍቅር ተይዞ አለማወቅ የከባድ ድብርት ምልክት ሊሆን ስለሚችል፤ ሁኔታው ከበድ ካለ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ማማከሩ እንደሚሻል ዶክተር ኤልያስ ገብሩ ያሳስባሉ።
በነገራችን ላይ… እኛ ማህበረሰባችን ውስጥ ለሁሉም የተቃራኒ ፆታ ሳቢነት ‘ፍቅር’ የሚል አጭር ስም የመስጠት ልማድ አለን አይደል?
ዶክተር ኤልያስ ግን ‘ቆም ብላችሁ መርምሩ’ ይላሉ ፡፡ መላመድ፣ መጎምጀት ወይም ደግሞ መማለል ሁሉ እውነተኛ ፍቅር አይደሉም! እነዚህ ከእውነተኛው የፍቅር ስሜት በታች ያሉ ዝቅተኛ ስሜቶች በመሆናቸው፤ እንደ እውነተኛ ፍቅር እንዳንቆጥራቸው ባለሙያው ይመክራሉ።
ሣራ ዮሐንስ
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
ለስነ-ልቦናዎ- የፍቅር ስሜት ማጣት እና መንስኤዎቹ
