የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰተው የመብራት መቆራረጥ የቴክኒክ ብልሽቶች ብቻ ሳይሆኑ የስርቆት ወንጀሎችም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አስታወቀ።
የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ከኤትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቁይታ እንደገለጹት፣ በተለይ የመዳብ ኬብሎችና የትራንስፎርመር ዘይቶች ላይ የሚፈጸመው ስርቆት ተቋሙንና ደንበኞችን ለከፍተኛ እንግልት እየዳረገ ይገኛል ተብሏል።
ይህ ድርጊት የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ፣ ተቋሙ የተሰረቁትን ንብረቶች ለመተካት ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጣና የጥገና ጊዜው እንዲራዘም እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያረጁ መስመሮችን በአዳዲስ የመተካት ስራ በስፋት እየተሰራ ሲሆን፣ ይህ ስራ በሚከናወንበት ወቅት በታቀደ መልኩ መብራት ሊጠፋ እንደሚችል አንስተዋል ።
የአየር ሁኔታ ለውጥ ማለትም ኃይለኛ ዝናብና ንፋስ በሚኖርበት ወቅት የመስመሮች መላተም እንደሚከሰትና ይህም ለድንገተኛ ብልሽት ምክንያት እንደሚሆን አቶ አንዋር ከጣቢችን ጋር በነበራቸው ቁይታ ገልጸዋል።
ተቋሙ እንደነዚህ ያሉ ድንገተኛ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት የጥገና ቡድኖችን በየአካባቢው ቢያሰማራም፣ የከተማዋ ስፋትና የመሠረተ ልማቱ ውስብስብነት ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው አቶ አንዋር ተናግረዋል።
በመጨረሻም፣ ህዝቡ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥበቃ እንዲያደርግና አጠራጣሪ ድርጊቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የመሠረተ ልማት ዕድሳቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለበዓላትና ለሀገራዊ ፈተናዎች ወቅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ኃላፊው ቃል ገብተዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም
