የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚቀጥለው ሳምንት በኒውዮርክ በሚካሄደው 81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉት የኢራን ዋና ልዑካን ቡድን አባላት ቪዛ መፍቀዱን አስታውቋል።
በቪዛው ከተካተቱት መካከል የኢራን ፕሬዝዳንት መስኡድ ፔዜሽኪያን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ይገኙበታል።
አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተናጋጅ አገር በመሆኗ ቪዛውን ለመስጠት ብትገደድም፣ ለኢራን ልዑካን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።
ልዑካኑ እንቅስቃሴያቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት፣ በኢራን ኢምባሲ/ልዑክ ጽህፈት ቤት እና ወደ ኤርፖርት በሚወስደው መንገድ ብቻ የሚወሰን ሲሆን፣ የቅንጦት ዕቃዎችን የመግዛት እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ቢቢሲ እንዳለው ውሳኔው የተላለፈው በሁለቱ አገራት መካከል ላለፉት ሰባት ወራት የዘለቀው ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭትና ውጥረት ባልበረደበት እንዲሁም የሆርሙዝ የባህር መንገድ መዘጋት ቀውስ በፈጠረበት ወቅት ነው።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እና ለልዑካን ቡድናቸው በጉባኤው እንዳይሳተፉ ቪዛ መከልከሉ ታውቋል።
መስከረም 8/2019 ዓ.ም
አሜሪካ ለኢራን ከፍተኛ መሪዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ቪዛ ፈቀደች
