የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ “እኛ አሸናፊ ትውልድ ነን፤ ከፊታችን ያሉትን ውስብስብ ፈተናዎች በድል
በመወጣት የበለፀገችና ራሷን የቻለች ኦሮሚያን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት አለብን” ሲሉ አስገነዘቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የተሰጣቸውን ከፍተኛ የህዝብ አደራ ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፤ ህዝቡ ላሳየው አመኔታ ምስጋና በማቅረብ
የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በተሟላ ብቃትና ቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
አቶ ሽመልስ በንግግራቸው፤ የኦሮሞ ህዝብ ለማንነቱ፣ ለነፃነቱ፣ ለባህሉና ለማህበራዊ እሴቶቹ መከበር እጅግ ውድ የሆነ
መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰዋል።
ሆኖም ግን “የተገኘውን ድል ጠብቆ ማቆየት ብቻ በቂ አይደለም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ድሎችን አፅንቶ በሁሉም መስክ የበለፀገች ኦሮሚያን የመገንባት ድርብ ታሪካዊ ግዴታ በትውልዱ ጫንቃ ላይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ያለፉትን አስቸጋሪና ፈታኝ ምዕራፎች በፅናት ማለፋቸውን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ወደፊትም ቢሆን የሚገጥሙን ፈተናዎች ቀላል እንዳልሆኑና ከፊታችን ያለው ትግል እጅግ ውስብስብ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህን እንቅፋቶች ተሻግሮ አሸናፊ ለመሆን ደግሞ የማይናወጥ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም “እኛ አሸናፊ ትውልድ በመሆናችን የህዝባችንን ብሩህ ተስፋና እጣፈንታ ለመወሰን በእውቀት፣
በክህሎትና በከፍተኛ አቅም ላይ ተመስርተን መስራት አለብን” ያሉ ሲሆን፤ የቀደመው ታሪካዊ ዓላማችን አንድነታችንን ይበልጥ
የሚያጠናክርና አብሮነታችንን የሚያፀና ሊሆን እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም፣ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ተልዕኮ እጅግ ግዙፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በልፋትና በፅናት የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ ለማስቀጠልና የተያዘውን ራስን የመቻል ግብ ዳር ለማድረስ፣ በየዓመቱ አዳዲስ ድሎችን በስራ እያስመዘገቡ መጓዝ የግድ መሆኑን አሳስበዋል።
ልዑል ወልዴ
መስከረም 18/2019 ዓ.ም
