ለከፍተኛ ትምህርት በሚል ወደ ሕንድ ያቀኑ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ።

በህንድ የሚማሩ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ዉስጥ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ያሉበትን ሁኔታ ሲናገሩ፣የምግብ መግዣም ሆነ ከሳኒታይዘር ጀምሮ ኮሮናን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶች መግዣ ሳይቀር መቸገራቸዉን ተናግረዋል፡፡

ተማሪ ብሩክና ተማሪ ሃጎስ በስተዲ-ኢን-ኢንድያ ለትምህርት እድል አግኝተዉ ወደ ህንድ ሲያቀኑ በመጀመሪያ ሁሉም ወጫቸዉ እንደሚሸፈንና የኪስ ገንዘብም እንደሚሰጡ ተነግሯቸዉ እንደነበር ያነሳሉ፡፡

ከሄዱ በኋላ የኪስ ገንዘብ እንደሌለዉ ተነግሯቸዉ ትምህርታቸዉን መከታተል ቀጥለዉ ነበር፡፡

ተማሪዎቹ እንደሚሉት ታዲያ አሁን ችግሩ የከፋ ሆኗል፤በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በተፈጠረዉ ቀዉስ ያሉባቸዉ ዩኒቨርስቲዎች በቂ ምግብ እያቀረቡላቸዉ አለመሆኑንና የሚያስፈልጋቸዉን ነገሮች ለመግዛት ምንም አይነት ገንዘብ እጃቸዉ ላይ እንደሌለ በመግለጽ፣ ከቤተሰብም ማስላክ አልቻልንም፣ ኤምባሲም ጠይቀን መልስ አጣን ሲሉ ነግረዉናል፡፡

ተማሪ ፍቅሩና ተማሪ ቤኛም ተመሳሳይ ችግራቸዉን ገልጸዉልናል፡፡

የተማሪዎቹን ቅሬታዎች ይዘን ጥያቄ ያቀረብንለት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በበኩሉ ስለሚባለዉ ነገር እዉቅና የለኝም ብሏል፡፡

በሚንስቱሩ የመምህራንና ተማሪዎች ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በላይ፣ “እኛ በግለሰብ ደረጃ ክፍያ አንፈጽምም፤በኤምባሲ በኩል ነዉ እንዲደርሳቸዉ የሚደረገዉ፤ እስካሁንም እነዚህ ቅሬታዎች እኛ ጋር አልመጡም ብለዉናል፡፡

እስካሁን የመጣዉ የአንድ ሰዉ ቅሬታ ነዉ እርሱም ደብዳቤ ሳይዝ የሄደ ነዉ ይስተካከላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን የኪስ ገንዘቡን ይሰጣቸዉ የነበረዉ የሚማሩበት ዩኒቨርስቲ ከሆነ የሚመለከተዉ የህንድን መንግስት እንጂ እኛን አይደለም፤እኛ ግን በኤምባሲዉ በኩል የተለመደ የ218 ዶላር የኪስ ክፍያችንን እየፈጸምን ነዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ ግን ለኤምባሲዉ ደብዳቤ ጽፈዉም ምላሽ እንዳላገኙ ነዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የምንበላዉ ምግብም ሆነ ክፋያዉን ያቅርብ እንጅ ብንታመም መታከሚያ ገንዘብ እጃችን ላይ የለንም የአገራችን መንግስት ሊደርስልን ይገባል ሲሉ እየጠየቁ ነዉ፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *