ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ሳይገናኝ ወደ ክልሉ ይሄድ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ላይ እንዲገናኝ መደረጉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ሳይገናኙ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲሰራጭ የነበረውን ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ አንድ ማዕከል እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም የትግራይ ክልልን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችም አሁን ላይ የኤሌክትረክ ኃይል የሚያገኙት ከብሔራዊ የኃይል ቋት መሆኑን ነግረውናል።
ከዚህ በፊት ወደነዚህ አካባቢዎች ይደረስ የነበረው የኤሌትሪክ ኃይል ከማዕከሉ የኃይል ቋት ጋር የተገናኘ ባለመሆኑ ለኃይል ብክነትና ኪሳራ ይዳርግ እንደነበርም አንስተዋል።
በመሆኑም ወደ ብሔራዊ የኤሌትሪክ ኃይል ቋት እንዲገቡ መደረጉ ችግሩን እንደሚፈታም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከጦርነቱ በፊት ወደ ትግራይ ክልል ይሄድ የነበረው የኤሌትሪክ ኃይል ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ያልተገናኘ በመሆኑ ለቁጥጥር አመቺ እንዳልነበር በተደጋጋሚ መነሳቱ አይዘነጋም።
በአባቱ መረቀ
ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም
