የዘንድሮው የከተራ በዓል በባቱ ደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል ተባለ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የጥምቀት የከተራን በዓል በባቱ ደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

በባቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የአርት ኢንዱስትሪ ባለሙያ አቶ ዘውገ በላይ ፤በዓሉን በተመለከተ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ የጥምቀትን በዓል በደምበል ኃይቅ ማክበር የተጀመረው ከጥንት ጀምሮ መሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ኃይቁ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ባለመነገሩ በሚፈለገው ደረጃ ሳይተዋወቅ መቆየቱን አስታውቀዋል።

ከፊታች ቅዳሜ የሚከበረውን የጥምቀት የከተራ እለት ላይ የሚሳተፉ የበዓሉ አክባሪዎችም ሆነ ጎብኚዎችን ለመጨመር በክልሉ የቱሪዝም ኮሚሽን አማካኝነት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ በሃይቅ ላይ እንደመከበሩ ለዚህ አገልግሎት የሚሆኑ 100 የሞተር ጀልባዎችና 150 በእንጨት የሚሰሩ ጀልባዎች ተዘጋተዋል ብለዋል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ለሚመጣው የባሉ ተሳታፊ እንዲሁም ጎብኚዎች ሆቴሎች ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የጠቀሱት አቶ ዘውገ፤ የተዘጋጁት ሆቴሎች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ሥራዎች ቀደም ተብሎ መሰራቱንም ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡

ሰላምና ፀጥታንም በተመለከተ በሰላም እንዲከበር ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሽዋ ዞን ከባቱ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ለቱሪስት መስህበነት ተመራጭ ከሆኑ ስፍራዎችና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የስምጥ ሸለቆ ኃይቆች አንዱ ነው።

ደምበል ኃይቅ በውስጡ ገሊላ፣ ደብረሲና፣ ደብረፂዮን፣ ጠደቻና ፉንድሮ የተሰኙ ደሴቶች ያሉት ሲሆን፤ በደሴቶቹ ላይ የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ገዳማት ይገኛሉ።

ከአምስቱ ገዳማት አቡነ ተክለሃይማኖትና ደብረ ጽዮን ከደሴታቸው በመውጣት ሦስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል አቋርጠው ምድር ላይ በማክበር ብቸኛ ያደርጋቸዋል።

ልኡል ወልዴ

ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *