በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው÷ አየር መንገዱ በዛሬው ዕለት ያስጀመረው የሀይድራባድ ቀጥታ በረራ የሁለቱን ሀገራት ትስስር የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በዓለም ከ140 በላይ መዳረሻዎች እንዳሉት አስታውሰው÷ ከአዲስ አበባ ሀይድራባድ ቀጥታ በረራ መጀመር በሀይድራባድ ላሉ በርካታ አፍሪካዊያን አማራጭ ትራንስፖርት እንደሚሆን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ ቀደም ሲል ወደ ከተማዋ መብረር እንደጀመረና በመንገደኞች የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጸው÷ በረራው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ የራሱን ድርሻ የሚጫወት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሺሪ አኒል ኩመር በበኩላቸው÷ ሀይድራባድ ለህንድ ወሳኝ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ በመሆኗ በረራው ለሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በረራው ሀይድራባድን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከተሞችንም በማስተሳሰር በትራንስፖርት ዘርፉ ትልቅ ድርሻ ይጫወታል ማለታቸውን ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል፡፡
ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
