ፖርቹጋላዊው የሊቨርፑል ኮከብ ዦታ ባጋጠመው የመኪና አደጋ በ28 ዓመት ዕድሜው ከትናነትና ወዲያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ አብሮት የነበረው ታናሽ ወንድሙ አንድሬ ሲልቫም በአደጋው አብሮት ህይወቱ አልፏል፡፡
አሳዛኙ ክስተት ያጋጠማቸውም በስፔን ዛሞራ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ አብሮት የሞተው አንድሬ ልክ እንደ ታላቅ ወንድሙ ሁሉ እሱም ፕሮፌሽናል ተጨዋች የነበረ ሲሆን በፖርቹጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚወዳደረው ፔናፊሌ ክለብ ነበር የሚጫወተው፡፡
አደጋው ባጋጠመው ወቅት ዲዬጎ ዦታ ወንድሙን ይዞ ሎምባርጊኒ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከረ ነበር፡፡ በመሀል የመኪናዋ ጎማ በመብረሩ መንገዱን ስቶ በመውጣት ከሌላ መኪና ጋር ሊጋጭና ይህንንም ተከትሎ መኪናዋ በእሳት በመያያዟ ሁለቱም ወንድማማቾች ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
በ28 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ዲዬጎ ዦታ ከረጅም ዓመታት ፍቅረኛው ሩት ካርዶሶ ጋር ጋብቻውን የፈፀመው ከሁለት ሳምንታት በፊት ጁን 22 ነበር፡፡ የጋብቻ ስነ-ስርዓታቸውን የሚያሳዩ ፎቶዎችንም በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆቹ ላይ ሲያጋራ ነበር፡፡ የአርሰናሉን ኮከብ ዴክላን ራይስን ጨምሮ በርካታ ተጨዋቾችና አድናቂዎቹም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶቻቸውን ሲያጋሯቸው ነበር፡፡ ጥንዶቹ ምንም እንኳን ጋብቻቸውን በይፋ የፈፀሙት በቅርቡ ቢሆንም ቀደም ሲል ግን ሶስት ህፃናት ልጆችን ማፍራት ችለው ነበር፡፡
ባለፈው የውድድር ዓመት ከሊቨርፑል ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው አጥቂው ከፖርቹጋል ብ/ቡድን ጋርም ከሳምንታት በፊት የኔሽንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ በ2019 ፖርቹጋል ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄን ዋንጫ ስታነሳም የቡድኑ አባል ነበር፡፡ ለሀገሩ ብ/ቡድንም በድምሩ 49 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡
የዲዬጎ ዦታን ህልፈት ተከትሎ የፖርቹጋሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ሉዊ ሞንቴኔግሮን ጨምሮ በርካቶች ሀዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
ምስጋናው ታደሰ
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም
