“ጣቢያው ባለቤት ያለው አይመስልም፤ የህልውናው ጉዳይ አሳስቦናል” የድርጅቱ ጋዜጠኞች

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሠራተኞች የተቋሙ ህልውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናገሩ፡፡
አጠቃላይ የተቋሙ እንቅስቃሴ በመዳከሙና ህልውናው አሳሳቢ በመሆኑ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው እንዳስጨነቃቸው የድርጅቱ ጋዜጠኞች ነግረውናል፡፡

ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የድርጅቱ ጋዜጠኞች ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ በተቋሙ ውስጥ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልፀው፣ ለአብነትም ደመወዝ በሰዓቱ እንደማይከፈላቸው፣ ይህም ተደጋግሞ የሚስተዋል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ላለፉት ሦስት አመታት የተቋሙ ፊዚካልና ፋይናንሻል የስራ አፈጻጻም፣ እንዲሁም የሰራተኛውም ሆነ የአመራሩ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዶ እንደማያውቅ የገለፁት ጋዜጠኞቹ “በይፋ ፈርሷል ለመባል ጫፍ ላይ ነው ያለው” በማለት ድርጅቱ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

የድርጅቱ ባለቤት የነበረው የቀድሞው የደቡብ  ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከፈረሰና አራት የተለያዩ ክልሎች ከተዋቀሩ በኋላ ክልሎቹ እንደየ ድርሻቸው ለተቋሙ በጀት የሚመድቡበት አሰራር የተዘረጋ ቢሆንም ተግባራዊ ባለመሆኑ ችግሮቹ መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የሲዳማ ክልል የራሱን ብዙሃን መገናኛ በመመስረቱ በጀት ለመመደብ ፍቃደኛ አለመሆኑን፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚጠበቅበትን እያዋጣ እንዳለሆነ የሚናገሩት ጋዜጠኞቹ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግን ከሚጠበቅበት በላይ በማዋጣት ለማገዝ እየሞከረ ነው ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትየጵያ ክልል በበኩሉ ከተመደበለት ኮታ በታች ቢሆንም በጀት እያዋጣ እንደሆነ ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች  ምክንያት ድርጅቱ ህልውናው እንደሚያሰጋና ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው አሳሳቢ መሆኑን ነው ጋዜጠኞቹ የገለፁት፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደተቋሙ ም/ ስራ አስፈፃሚና የይዘት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዘላለም ገነሞ ስልክ ብንደውልም ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

አዲስዓለም አበበ

ሀምሌ 14/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *