የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የመፍረስ አደጋ ውስጥ አይደለም ሲሉ የተቋሙ ሃላፊ ተናገሩ፡፡

ከዚህ ቀደም የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሠራተኞች የተቋሙ ህልውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ስጋታቸውን እንደነገሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የድርጅቱ ሰራተኞች አጠቃላይ የተቋሙ እንቅስቃሴ በመዳከሙና ህልውናው አሳሳቢ በመሆኑ ቀጣይ ዕጣ ፈንታችን አስጨንቆናል ማለታቸውን ተከትሎ የጣቢያውን ሃላፊ ስለጉዳዩ ጠይቀናል፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ተወካይና ም/ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ገነሞ ለዚህ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ የመፍረስ አደጋ ውስጥ አለመሆኑን በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ብለዋል፡፡ የፌደራል መንግስትም ሆነ አራቱ ክልሎች ድርጅቱ እንዲቀጥል ፍላጎት አላቸው ሲሉም አክለዋል፡፡

በተቋሙ ላይ የሚነሱ ስጋቶችን እንደሚረዱ የገለፁት ተወካዩ፣ የቀድሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአራት ክልሎች መዋቀሩን ተከትሎ የበጀት ጉድለት እንዳጋጠመ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተመደበላቸውን ኮታ እያዋጡ ነው ያሉ ሲሆን፣ የሲዳማ እና የደቡበ ምዕራበ ኢትዮጵያ ክልሎችም ቢሆኑ አናዋጣም በሚል ሳይሆን ካጋጠማቸው የበጀት እጥረት አኳያ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ለ2018 በጀት ዓመት ግን የደቡበ ምዕራበ ኢትዮጵያ ክልል በምክር ቤት በጀቱን አስወስኖ ለተቋሙ ሰጥቷል ያሉት አቶ ዘላለም ከሲዳማ ክልል ጋርም እየተነጋገሩ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ በ2018 ዓ.ም ከአምናው በተሻለ ደረጀቱ ካለበት ችግር ይወጣል የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡

የሰራተኞች ደሞዝ መዘግየትን በተመለከተ ችግሩ መኖሩን አምነው ችግሩን ለማስተካከል እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

አዲስአለም አበበ

ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *