በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ ዳርጎ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወደ 50 የሚጠጉ ወታደሮች ተገድለዋል ተብሏል።
የአካባቢው ምንጮች እንደተናገሩት፤ ወደ 1መቶ የሚጠጉ ታጣቂዎች ወታደሮቹን ገድለው ዝርፊያ ፈፅመዋል።
ከመከላከያ ኃይሉ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም ጥቃቱን ያደረሰዉ ቡድን በምዕራብ አፍሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታዎችን ለሞት የዳረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፏል።
ቡርኪናፋሶ አሁንም እየተባባሰ በቀጠለዉ ከደህንነት ቀውስ ጋር ትግሏን ቀጥላለች፡፡
እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል በተለይም ከዋና ከተማው ርቀው የሚገኙትን ገጠራማ አካባቢዎች ተቆጣጥረዋል።
ግጭቱ ከ2022 ጀምሮ ሁለቱን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውዥንብር አስከትሏል።
ጊዜያዊው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ፤ አጋሮቻቸውን እና ወታደራዊ አመራሮችን ቢቀያይሩም የአክራሪዎችን ጥቃት መስፋፋት ለማስቆም ተቸግረዋል።
የደረሰዉ ጥቃት በክልሉ እየጨመረ የመጣውን አለመረጋጋትና በጣም ተለዋዋጭ በሆነው ግጭት ቀጣና ውስጥ በወታደሮችም ሆነ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ያሳያል ተብሏል።
ኤርሚያስ ገረመዉ
ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም
