የማሊ ባለስልጣናት በስልጣን ላይ የሚገኘውን ወታደራዊ መንግስት ለመገልበጥ አሲረዋል የተባሉ ሁለት ደርዘን ወታደሮችን ማሰራቸውን ምንጮቼ ነግረዉኛል ሲል ኤኤፍፒ ነዉ የዘገበዉ፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንድ ከፍተኛ ጄኔራል የሚገኙ ሲሆን፤ይህም በሰራዊቱ ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ቅሬታ እና በማሊ ውስጥ የቀጠለውን አለመረጋጋት የሚያሳይ ነዉ ተብሏል፡፡
ወታደራዊዉ መንግስት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በ2020 እና 2021 በተካሄዱ ተከታታይ መፈንቅለ መንግስቶች ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊት ተቋማትን ለማተራመስ ከሚደረግ ሙከራ ጋር በተያያዘ እስራት ተካሂዷል፤ቢያንስ 20 የሚሆኑ ሰዎች ታስረዋል ሲሉ አንድ የማሊ የደህንነት ምንጭ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ሌላ ምንጭ የማተራመስ ሙከራ መኖሩን አረጋግጠን አስፈላጊውን እስራት ፈጽመናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከ2012 ጀምሮ ማሊ በተለያዩ ግንባሮች በችግር ስትታመስ ቆይታለች።
ከአልቃይዳ ወይም ኢስላማዊ መንግስት ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በሳሄል ቀጣና ውስጥ የኃይል ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
ወንጀል እና ግጭቶችም በስፋት የሚታዩ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚም በአስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ወታደራዊዉ መንግስት ሀገሪቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ነጻ መሆን አለባት በሚል ለፈረንሳይ ጀርባውን ሰጥቷል።
እንደ ጎረቤት ሀገራት ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ሁሉ ከሌሎች አዳዲስ አጋሮች ጋር በተለይም ከሩሲያ ጋር ግንኙነት መስርቷል።
በሐምሌ ወር በወታደራዊዉ መንግስት የተሾመው የሕግ አውጪ አካል፤ የማሊውን ጁንታ መሪ ጄኔራል አሲሚ ጎይታን ለአምስት ዓመታት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡
ወታደራዊው መንግስት በመጀመሪያ ወደ ሲቪል አስተዳደር በመጋቢት 2024 እመለሳለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ነበር ሲል የዘገበዉ ፍራንስ 24 ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም
