ኩባንያው በአገር ውስጥ እየሰጠ ከሚገኘው አገልግሎት በተጨማሪ ለውጭ ገበያው አገልግሎት ለመስጠት ማሰቡን አስታውቋል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፥ ከኢትዮጵያ ገበያ ውጭ አዳዲስ መፍትሄዎችን ይዞ ለመቅረብ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተጠናቀቀውን ሊድ የተሰኘ የሶስት አመት ስትራቴጂ የሚተካ አዲስ የሶስት አመት ዕቅድ ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው ይህን አዲስ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ “ቀጣዩ አድማስ” ሲል ስያሜ የሰጠው ሲሆን፤ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብሏል።
ይህ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ እስከዛሬ ከነበሩት የኩባንያው ዕቅዶች የተለየ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ወደ ውጭ ገበያም ወጥቶ ለመስራት ዕቅድ መያዙን አንስተዋል።
ዲጂታል አፍሪካ ትራንስፎርሜሽን 2063 አንደኛው ይህን ዕቅድ ወደ ሌሎች አገራት ገበያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ ውስጥ ኩባንያው በኢትዮጵያ ገበያ መሪ ሆኖ መቀጠል አንደኛው ዕቅዱ መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ ይህንን መሪነት ወደ ውጭ ገበያም ለማስፋፋት ታስቧል ብለዋል።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም
