ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ውስጥ 125 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቴክ ስታርት የተሰኘ የኦንላይን ስልጠና ፕሮጀክት ይፋ አድርጎል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቴክ ስታርት ዕድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆናቸው ወጣቶችን በአማዞን ድረ-ገጽ የክህሎት ማዕከል በኩል መሠረታዊ የክላውድ ስልጠና እና ቀጣይነት ያለው የዌብ ሰርቪስ ስልጠና እድል እንዲያገኙ የሚያመቻች ዲጂታል ስልጠና ነው ተብሏል ።
ፕሮጀክቱ 125 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል እና ክላውድ ቴክኖሎጂ ለማሰልጠን ያለመ ሲሆን ከ18 አመት በላይ ለሆኑ ወጣቶች መሠረታዊ የክላውድ ስልጠና መስጠት፣ በዌብ ሰርቪስ ቀጣይነት ያለው ስልጠና እንዲያገኙ ማስቻል እና ኢትዮጵያ ወደ ቴክኖሎጂ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ የመደገፍ ዓላማዎችን የያዘ እንደሆነ ተነግሯል ።
የፕሮግራሙን ይፋ መደረግን ተከትሎ የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄሌፑት እንዳሉት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴክኖሎጂ ስልጠና ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣ አስደናቂ ክህሎት ያላቸውን የቴክኖሎጂ ኮከቦች ለማፍራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስራ አስፈፃሚው የወጣቶቻችንን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ሁሉን አሳታፊ፣ በፈጠራ የበለጸገች እና ለነገ ተወዳዳሪ የሆነች ኢትዮጵያን እንገነባለን ብለዋል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሰው ሀብት አስተዳደር ዋና ኃላፊ ፀዳለ ተስፋዬ በበኩላቸው መሰል ስልጠናዎች የአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አስተዋጽኦ የሚያበርክቱ ኢንቨስትመንቶቻችን ናቸው ብለዋል።
የስልጠናው ምዝገባ በቅርቡ የሚጀምር መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለመመዝገብ ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያዎች ይፋ እንደሚደረጉ ተመላክቷል።
አቤል እስጢፋኖስ
ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም
