5ኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል ተባለ ፡፡

የዘንድሮ “የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት” ከወትሮ በተለየ መልኩ የኦሮሚያን እንዲሁም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት ለአለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ በሚቻልበት መልኩ ይከበራል ሲል የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ይህን የገለፀው የዘንድሮውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት እና የኢሬቻ በዓል አከባበር አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ በመግለጫቸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ አራት ዓመት ቢሞላውም በክልሉ ውስጥ ያለውን የቱሪዝም ሀብት የማስተዋወቅ ስራዎች መስራቱን ገልጸዋል።

ሆኖም ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት መርሃ ግብር በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በመርሃ-ገብሩ የኦሮሚያን ይጎብኙ ብራንድ ማስተዋወቅ፣ የወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ የቁንጅና ውድድር፣ የቱሪዝም ኤግዚቢሽንና ሌሎች በርካታ ኹነቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

የሰላምና የይቅርታ በዓል የሆነው ኢሬቻም እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ የሚከበር በዓል መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በእለታቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በዓሉን በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ተገኝተው የሚታደሙ መሆኑን አንስተዋል።

በኩነቱ ከሚሳተፉት የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቦርዶች እና የቱሪዝም ክፍሎች መካከል ከኬንያ ፣ ናሚቢያ ፣ ሩዋንዳ ፣ ብሩንዲ ፣ ኡጋንዳ እና ጅቡቲ ይገኙበታል።

በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶችን በቆየው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህላችን ተቀብሎ ከማስተናገድ ባሻገር በዓሉ ይዞ ከሚመጣው እድል የአዲስ አበባና የቢሾፍቱ ከተሞች ነዋሪዎችና ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ የኦሮሚያን የተለያዩ የቱሪዝም መስቦችን፣ ደማቅ ባህላዊ ቅርሶችን፣ እሴቶችን ለማሳየት ልዩ መድረክ ይሰጣል ተብሏል።

ልኡል ወልዴ

መስከረም 9/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *