ውድድርን ማዕከል ባደረገው የዓለም ገበያ ውስጥ ተፎካካሪ ለመሆን የተቀመጡ ደረጃዎችን በተገቢው መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ እና አካባቢ ግንባታ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ገልፀዋል፡፡
ይህን የጥራት አሰራር በቋሚነት ለመተግበር ማወቅ ፣መለማመድ እንዲሁም የራስ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ለጣቢያችን አስረድተዋል፡፡
የጥራት ጉዳይ ባህል ተደርጎ መወሰድ ስላለበት ከመሠረቱ በሂደት ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ህግ አውጪውም ሆነ አስፈፃሚውን አካል ጨምሮ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ፕሮፌሰር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ህዝቡም መብቱን መጠየቅ እና ከደረጃ በታች ለገበያ ቀርበው የተገኙ ምርቶችን በማጋለጥ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጲያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እስከ አሁን ከ12ሺህ በላይ ለሆኑ ምርቶች ደረጃዎች አስቀምጧል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም
