ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የምሸጠዉ የእንስሳት ኢንሹራንስ ዋስትና ለሞቱ የአርብቶ አደሮች እንስሳት ካሳ የሚከፈልበት አሰራር እንደሌለ ሊታወቅልኝ ይገባል ብሏል።
ግብርና ሚኒስቴር በአመት ሁለት ዙር የአርብቶ አደር የእንስሳት ኢንሹራንስ ዋስትና እንደሚሸጥ ይገልፃል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ኘሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጀማል አልዩ፤ኢንሹራንሱ የእንስሳት ግጦሹ (ሳሩ) የሚገባ መሆኑን ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል።
የድርቅ አካባቢዎች እንዲለይ እየተሰራበት ባለዉ ሳተላይት ጠቋሚነት የአርብቶ አደሩ አካባቢ ለግጦሽ የሚሆን ሳር እያለቀ መምጣቱን በሚጠቁመዉ መሠረት ለእንስሳቱ መኖ እና መድኃኒት መሰል ግብዓቶች እንዲገዙ ለአርብቶ አደሩ የሚከፈል ኢንሹራንስ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የኢንሹራንሱ ፋይዳ እንስሳት በድርቁ እንዳይሞቱ እንዲሁም እንዳይጎዱ የሚያደርግ ነዉ፤ ዋስትናዉ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አቶ ጀማል ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ድርቁ በተከሰተበት ጊዜ ለእንስሳቱ በተገባ ኢንሹራንስ መሠረት ለአርብቶ አደሩ እንዲገዛ የሚሰጠውን ገንዘብ በአግባቡ ለእንስሳቱ ቀለብ ሳያዉል እንስሳቱ ቢያልፉ ኢንሹራንሱ ተጠያቂ አለመሆኑን ይታወቅ ብለዋል።
ለሞቱ እንስሳት ይከፈላል የሚል የኢንሹራንስ አሰራር አለመኖሩን አስረድተዋል።
አቶ ጀማል የአርብቶ አደር እንስሳት ኢንሹራንስ አሰራር በአርብቶ አደሩ ዘንድ መረዳት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ቁምነገር አየለ
ህዳር 01/2018 ዓ.ም
