ከቬንዝዌላ ጋር ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት አሜሪካ በፓሲፊክ ውቅያኖስ በፈጸመችው የቅርብ ጊዜ ጥቃት 4 ሰዎችን ገደለች

አዲሱ ጥቃት በምስራቅ ፓሲፊክ እና በካሪቢያን አካባቢ በሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ላይ አሜሪካ በወሰደችው እርምጃ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ወደ 100 አድርሶታል፡፡

በምስራቅ ፓሲፊክ ውቅያኖስ የተፈጸሙት እነዚህ ሦስት የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች፤ አሜሪካ ለቬንዝዌላ ቅርብ በሆኑት በትሪኒዳድ እና ቶባጎ ወታደራዊ ኃይሏን እያጠናከረች ባለችበት ወቅት የተከሰቱ ናቸው።

አሜሪካ በላቲን አሜሪካ ወታደራዊ ኃይሏን ማጠናከሯን በቀጠለችበት እና የቬንዝዌላን የነዳጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ካዋለች ከቀናት በኋላ፤በምስራቅ ፓሲፊክ ውቅያኖስ በጀልባዎች ላይ በፈጸመችው አዲስ ጥቃት ስምንት ሰዎችን መግደሏን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ጦር ደቡባዊ ዕዝ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፤ በመከላከያ ጸሃፊው ፒት ሄግሴዝ ትእዛዝ ሰኞ ዕለት በአለም አቀፍ ውሃ ላይ በሚገኙ ሶስት ጀልባዎች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

በድምሩ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ደቡባዊ ዕዝ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

መግለጫው፤በመጀመሪያው ጀልባ ሶስት፣ በሁለተኛው ሁለት እንዲሁም በሶስተኛው ሶስት ሰዎች ተገድለዋል ያለ ሲሆን፤ ሟቾቹ ከዕፅ ዝውውር ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ገልጾ ለዚህ ግን ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረበም።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በፓሲፊክ ውቅያኖስ እና በቬንዝዌላ አቅራቢያ በሚገኘው የካሪቢያን ባህር ውስጥ በደርዘን በሚቆጠሩ ጀልባዎች ላይ በተፈጸሙ ተመሳሳይ የአሜሪካ ጥቃቶች ቢያንስ 90 ሰዎች ተገድለዋል፤ ይህንንም የአለም አቀፍ ህግ ባለሙያዎች በአሜሪካ ጦር የተፈጸመ ‹‹ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ››ሲሉ ይተቹታል።

ቬንዝዌላ ጥቃቶቹ እና የአሜሪካ ወታደራዊ ከበባ ዓላማው የውጭ ኃይሎች የቬንዝዌላን እጅግ ብዙ የነዳጅ እና የጋዝ ሀብት እንዲዘርፉ ለማስቻል እንደሆነ ገልጻለች።

ለዚህም ማስረጃ ስታቀርብ፤የአሜሪካ ኃይሎች ባለፈው ሳምንት በቬንዝዌላ የባህር ዳርቻ የነዳጅ መርከብን በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች ‹‹ነዳጁን እኛ የምንወስደው ይመስለኛል›› ማለታቸዉን በማስታወስ ነዉ፡፡

ሱፊያን አህመድ

ታህሳስ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *