ረጂ ተቋማት በጥቂት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋቸው ሊስተካከል እንደሚገባ ተገለጸ

በአዲስ አበባም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቢኖሩም ለጋሽ ተቋማት ግን ትኩረት የሚያደርጉት የተወሰኑት ላይ ብቻ እንደሆነ ተነስቷል፡፡

ይህ የተገለጸው ዝግባ የህጻናትና አረጋውያን የበጎ አድራጎት ድርጅት ለተረጂዎች የገና በአል ድጋፍ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ ድርጅቱ የገና በአልን ምክንያት በማድረግ ወላጆቻቸዉን በሞት ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ህፃናት ፣ ጧሪ ደጋፊ ለሌላቸዉ አረጋዉያን፣ እንዲሁም በችግር ላይ ለሚገኙ ሴቶች የማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳት እና ቁሳቁስ ስጦታ አካሂዷል።

ታሕሳስ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በግዮን ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብር ላይ የቂርቆስ ክ/ከተማ የስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ጌታቸው በዚህ ወቅት ሲናገሩ፣ እስካሁን ድረስ ከውጭ ተቋማት ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳልተቀበሉና ድርጅቱ ሲመሰረትም መነሻ ሃሳቡ ማሕበረሰቡ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎችም ሁልጊዜም እየተረዱ የሚቀጥሉ ሳይሆኑ ድርጅቱ ዘላቂ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያመቻችላቸውና ይህም ለሰባት ዓመታት ያህል የሚከናወን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አካላት በተመሳሳይ ለሰባት ዓመታት ድጋፍና ስልጠና እየተሰጣቸው ሂደቱ እንደሚቀጥል አቶ ስለሺ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ለእርዳታ የሚሆነውን ገንዘብ ድርጅቱ ከሚፈጥረው የገቢ ማስገኛ ስራዎችና ከማሕበረሰቡ እንደሚያገኙ የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ሆኖም ለጋሽ ተቋማት ድጋፋቸው ወደተወሰኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ብቻ እንደሚያተኩርና ይህም ቢስተካከል የሚል ምክረ ሃሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ዝግባ የህጻናትና አረጋውያን የበጎ አድራጎት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እንደሚገኙ ገልጸው፣ ለጋሽ ተቋማት ድጋፋቸውን ለበርካቶች ለማድረስ ቢሞክሩ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አዲስዓለም አበበ

ታህሳስ 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *