የቬንዙዌላዋ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሜዳሊያዋን ለትራምፕ አበረከተች፡፡

የቬንዙዌላ የተቃዋሚ ቡድን መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ በዋይት ሃውስ በተካሄደ የግል ስብሰባ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያዋን ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማበርከቷን ገልጻለች።

ሁለቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ከተገናኙ በኋላ ማቻዶ ስትናገር “ዛሬ ለእኛ ለቬንዙዌላውያን ታሪካዊ ቀን ይመስለኛል” ብላለች።

ይህ ስብሰባ የተካሄደው የአሜሪካ ኃይሎች የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በካራካስ በቁጥጥር ስር አውለው በዕፅ ዝውውር ወንጀል ከከሰሷቸው ከሳምንታት በኋላ ነው።

ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት ምስጋናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ድርጊቱ “ድንቅ የሆነ የጋራ መከባበር መገለጫ” መሆኑን ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በ2024 በነበረው አወዛጋቢ ምርጫ ድል ማግኘቱን የሚናገረውን የማቻዶን ንቅናቄ እንደ አዲስ የሀገሪቱ መሪነት ለመቀበል እስካሁን ፍቃደኛ አልሆኑም።

በምትኩ ትራምፕ ግንኙነት እያደረጉ ያሉት የማዱሮ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ከነበሩትና በአሁኑ ወቅት የቬንዙዌላ ጊዜያዊ መሪ ከሆኑት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ጋር ነው።

ሆኖም ትራምፕ ከማቻዶ ጋር መገናኘታቸው “ትልቅ ክብር” መሆኑን ገልጸው፤እርሷንም “ብዙ መከራዎችን ያለፈች ድንቅ ሴት” ሲሉ ጠርተዋታል።

ማቻዶ ከዋይት ሃውስ ከወጣች በኋላ በበሩ ላይ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቿ በስፓኒሽ ቋንቋ ንግግር ያደረገች ሲሆን፤ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው “በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ መተማመን እንችላለን” ብላለች።

በኋላም ለጋዜጠኞች በእንግሊዝኛ እንደተናገረችው “የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያዬን ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት አበርክቻለሁ” ስትል፤ ይህም “ለእኛ ነፃነት ላሳዩት ልዩ ቁርጠኝነት የተሰጠ እውቅና ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሐመረ ፍሬው

ጥር 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *