ባፕቲስት ሚኒስትር እና የሲቪል መብቶች ተሟጋች የሆኑት ሬቨረንድ ጄሲ ጃክሰን በ84 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልፀዋል።
ቤተሰቦቻቸው ባወጡት መግለጫ “አባታችን አገልጋይ፣ መሪ፣ ለቤተሰባችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለተጨቆኑ፣ ድምፅ ለሌላቸው እና ችላ ለተባሉ ሁሉ ጭምር ዕውነተኛ አባት ነበር። እኛ እሱን ለዓለም አጋርተናል፤ በምላሹም ዓለም የሰፊው ቤተሰባችን አካል ሆኗል። በፍትህ፣ በእኩልነት እና በፍቅር ላይ ያለው የማይናወጥ እምነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አንቅቷል፤ እሱ የኖረለትን እሴቶች በማስቀጠል ትዝታውን እንድታከብሩ እንጠይቃለን” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ታዋቂ ሰው ጄሲ ጃክሰን እ.ኤ.አ. በ2017 በፓርኪንሰን በሽታ መያዛቸው ከታወቀ በኋላ፣ በቤተሰቦቻቸው ታጅበው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከግሪንቪል ደቡብ ካሮላይና የተገኙት ጄሲ ጃክሰን የፖለቲካ ሕይወታቸውን የጀመሩት በዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የቅርብ የሥራ ባልደረቦች ክበብ ውስጥ አብሮ በመሥራት ነበር።
ማርቲን ሉተር ኪንግ እ.ኤ.አ. በ1968 በተገደለበት ወቅት ጄሲ አብረውት የነበሩ ሲሆን፤ ቆየት ብሎም የዘር እኩልነት እንዲረጋገጥ ግፊት ለማድረግ ተማሪዎች የሚያደርጉትን የ”ሲት-ኢን” (sit-ins) ተቃውሞዎችን መርተዋል።
በተጨማሪም መራጮችን ለማሳተፍ እና ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን የሚሰራውን PUSH (People United to Save Humanity) እና ሬይንቦው ኮአሊሽን (Rainbow Coalition) የተባሉ ድርጅቶችን መስርተዋል።
እ.ኤ.አ. በ1984 እና በ1988 ለፕሬዝዳንትነት ቢወዳደሩም በመጨረሻም በፓርቲያቸው የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ሳይመረጡ ቀርተዋል።
ጄሲ ጃክሰን በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን በመቀጠል፣በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኩዌት ታስረው የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲፈቱ ግፊት አድርገዋል። እ.ኤ.አ. በ2000 ደግሞ የፕሬዝዳንታዊ የነፃነት ሜዳሊያ (Presidential Medal of Freedom) ተሸልመዋል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በይፋ ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በ2020 አሜሪካውያን “ከዚህ የተሻለ ይገባቸዋል” በማለት ተናግረው ነበር።
ምስጋናው ታደሰ
የካቲት 10/2018 ዓ.ም
