ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢስላማዊቷ ሪፐብሊክ ላይ አዲስ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ሁኔታዎችን እያጢኑ ነው በሚባልበት ወቅት፣ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ብታደርግ “በጣም ብልህነት” እንደሚሆን ኋይት ሃውስ አስጠነቅቁዋል።
የኋይት ሃውስ የፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮሊን ሌቪት በሰጡት መግለጫ፣ ትራምፕ አሁንም በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ዙሪያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሄ ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፤የእሳቸው አስተያየት የመጣው አሜሪካ ሁለተኛ የጦር መርከቧን ወደ ቀጠናው እያዘዋወረች ባለችበት እና በስዊዘርላንድ በተደረገው የአሜሪካ-ኢራን ንግግር ላይ መሻሻል መታየቱ በተዘገበ ማግስት ነው።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዕለት እንደዘገቡት ከሆነ፣ ትራምፕ ከአማካሪዎቻቸው ጋር የጥቃት አማራጮችን የተወያዩ ሲሆን፣ ጥቃቱም እስከ ቅዳሜ ድረስ ሊፈጸም እንደሚችል ተመልክቷል፤ ባለፈው በጋ የአሜሪካ ጦር በሶስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።
ቢቢሲ በአሜሪካ ካለው አጋሩ ሲቢኤስ ኒውስ (CBS News) ሰማሁ እንዳለው ከሆነ፣ ትራምፕ ጥቃት ስለመሰንዘር እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ አላሳለፉም፤ ውይይቱም እንደቀጠለ ነው። ሌቪት ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ብዙ ምክንያቶችን እና መከራከሪያዎችን ማቅረብ ይቻላል” ብለዋል።
ሰኔ ወር ላይ አሜሪካ የሰነዘረችውን ጥቃት በማስታወስ “ኢራን ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከአስተዳደራቸው ጋር ስምምነት ብታደርግ በጣም ብልህነት ይሆንላታል” ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳን ማክሰኞ ዕለት በጄኔቫ በተካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ላይ ትልቅ ለውጥ ባይታይም፣ ሁለቱም ወገኖች ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚወስዱ እርምጃዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የኒውክሌር ውዝግብን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ማዕቀፍ የሚሆኑ “መሪ መርሆዎች” ላይ ከአሜሪካ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ኢራን ገልጻለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ግን አሁንም መከናወን ያለባቸው ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ዋሽንግተን “መሻሻል ታይቷል” ብትልም ንግግሩን የምታሸማግለው ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሰይዲ፣ ድርድሩ በጋራ ግቦች እና በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ “በጥሩ መሻሻል ተጠናቋል” ብለዋል።
ሆኖም የኋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ዋሽንግተን እና ቴህራን በአንዳንድ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አሁንም “በጣም ተራርቀው” እንደሚገኙ ገልጸዋል።
“ኢራናውያን በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ በመሆኑም ፕሬዝዳንቱ ሂደቱ እንዴት እንደሚሄድ መከታተላቸውን ይቀጥላሉ” ብለዋል ሌቪት።
ሌቪት በእነዚህ ውሳኔዎች ላይ የእስራኤል ተሳትፎ ይኑር አይኑር ከመናገር ተቆጥበዋል።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 12/2018 ዓ.ም
