በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በይፋ በተከፈተውና አፍሪካን የማላቅ ዓላማ ባለው የ’Elevate Africa’ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ፣ ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለኢኮኖሚ እድገቷ እንደ ዋነኛ አቅም በመጠቀም በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን መዘጋጀቷ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለይም በ2010 በጀመረችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አማካኝነት መሠረታዊ ለውጦችን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
መንግስት ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለማዕድን እና ለቱሪዝም ዘርፎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም፤ እነዚህን ዘርፎች በዘመናዊ መንገድ ለማሳለጥ ቴክኖሎጂን እንደ ማዕከላዊ ምሰሶ መውሰዱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስትከተለው የነበረውን ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025’ ስትራቴጂን በማጠናቀቅ፣ አሁን ላይ ወደ ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030’ እየተሸጋገረች ነው ያሉት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ይህ አዲስ ምዕራፍ ከመሠረተ ልማት ወደ ዕድል ፈጠራ የመሸጋገር ዓላማ እንዳለው አብራርተዋል።
ትኩረቱም የቴሌኮም እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ወደ ተጨባጭ የሥራ ዕድል መቀየር፣ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን (ስታርታፖችን) ማበረታታት እና የሀገሪቱን ወጣት ተሰጥኦ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ማገናኘት እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፋዊ የዲጂታል ጉዞ ውስጥ ተመልካች ብቻ ሳትሆን፣ የወደፊቱን የኢኮኖሚ ዋና ተሳታፊ ለመሆን መነሳቷን የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዢው፤ እንደ ህንድ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን በትጋት እየሰራች መሆኑም ጠቁመዋል።
ገዢው ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗንና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በዚህ የለውጥ ጉዞ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስአለም አበበ
የካቲት 25/2018 ዓ.ም
