የአሜሪካ እና የኢኳዶር ኃይሎች የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመዋጋት ዘመቻ ጀመሩ

የአሜሪካ ደቡባዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፤ የአሜሪካ እና የኢኳዶር ኃይሎች በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ውስጥ “ሽብርተኛ” ተብለው በተፈረጁ ድርጅቶች ላይ ዘመቻ መጀመራቸውን አስታውቋል።

ደቡባዊ ዕዙ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ፣ ዘመቻው ሕገ-ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት ያለመ መሆኑን ቢገልጽም፣ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጠም።

ይህ መግለጫ የወጣው የኢኳዶር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦኣ፤ አሜሪካ በኢኳዶር የዕፅ ካርቴሎች ላይ እየተካሄደ ባለው “አዲስ ምዕራፍ” ጦርነት ውስጥ ከሚሳተፉ “የቀጣናው አጋሮች” አንዷ መሆኗን ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

እንደ ኖቦኣ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ኮኬይን 70 በመቶ የሚሆነው በኢኳዶር ግዙፍ ወደቦች በኩል የሚያልፍ ሲሆን፣ ይህም ሀገሪቱን ለአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች አትራፊ ቦታ አድርጓታል።

በተጨማሪም ሀገሪቱ በዓለም ትልቁ የኮኬይን አምራቾች ከሆኑት ኮሎምቢያ እና ፔሩ ጋር ትጎራበታለች።

ይህ የቅርብ ጊዜ ዘመቻ የተጀመረው፣ የኢኳዶር ሕዝብ በሀገሪቱ የውጭ አገር ወታደራዊ ካምፖች እንዲመለሱ የሚፈቅደውን የሕግ ማሻሻያ በሪፈረንዱም ውድቅ ካደረጉ ከአራት ወራት በኋላ ነው። ይህም አሜሪካ በምስራቅ ፓስፊክ ቀጠና ያላትን ተጽዕኖ ለማስፋፋት የነበራትን ተስፋ ያመከነ ነበር።

የሪፈረንዱሙ ውጤት፣ የተደራጁ ወንጀሎችን ለመዋጋት እና እየጨመረ የመጣውን አመፅ ለመቀነስ ለሚጥሩትና የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ አጋር ለሆኑት ለኖቦኣ ትልቅ ሽንፈት ነበር።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢኳዶር በዓለም ላይ ካሉ ዋና ዋና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መናኸሪያዎች አንዷ ሆናለች።

ሀና ሰይፉ

የካቲት 25/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *