በአነፍናፊ ውሾች የታገዘ የዱር እንስሳት ውጤቶች ሕገ-ወጥ ዝውውር መቆጣጠሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጀመረ

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከአፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ዝውውር ለመግታት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና አስጀምሯል።

ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆየው ይህ ሥልጠና ከታንዛኒያና ከኬንያ በመጡ ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን፤በዋናነትም በዱር እንስሳት ወንጀል ቦታ አያያዝ፣ በሰብዓዊ መብቶችና በምስክርነት አስረጂነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ በዘርፉ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው በአነፍናፊ ውሾች የታገዘ የቁጥጥር ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ይገኛል።

ቀደም ሲል በአየር መንገዱ ይስተዋሉ የነበሩ ውስንነቶች አሁን ላይ መቃለላቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ዝውውሩን በአስተማማኝ ሁኔታ በመከላከል ረገድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማይደፈር ደረጃ መብቃቱንና ለዚህም የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጊቱ የሀገር ደህንነት ስጋትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መሆኑን ያነሱት አቶ ኩመራ፤ የሥልጠናው ዋና ዓላማም እነዚህን ሕገ-ወጥ ተግባራት በዘላቂነት በመግታት የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።

መጋቢት 16/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *