የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ንግግር ‹‹በጣም በጥሩ ሁኔታ›› እየሄደ መሆኑን በመጥቀስ፤ የኢራን የኃይል ማመንጫዎችን ለማውደም የነበራቸውን ዕቅድ ለተጨማሪ 10 ቀናት ማራዘማቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተራዝሞ የነበረው እራሳቸው የቆረጡት የጊዜ ገደብ አሁን ወደ ሚያዝያ 6 ተገፍቷል፡፡
ኢራን በትራምፕ ውሳኔ ላይ እስካሁን በይፋ የሰጠችው ምላሽ ባይኖርም፤ ቴህራን ቀደም ሲል ዋሽንግተን ለተኩስ አቁም ስምምነት ላቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምላሽ እንድትሰጥ እየጠበቀች መሆኑን ገልጻ ነበር፡፡
በካቢኔ ስብሰባ ላይ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ አሜሪካ ለኢራን የ15 ነጥብ የሰላም ዕቅድ መላኳን አረጋግጠዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን በሰላም ስምምነቱ ላይ ካልተስማማች አሜሪካ ለኢራን ‹‹የከፋ ቅዠት›› እንደምትሆንባት ተናግረዋል።
ትራምፕ የኃይል ማመንጫ ጥቃቱን ማራዘማቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ወዲያውኑ ቀንሷል።
በታገደው የሆርሙዝ መስመር በኩል የሚያልፈው ዘጠኝ አስረኛው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ወደ እስያ አገራት የሚሄድ ነው፡፡
በሌላ በኩል እስራኤል ከኢራን የተተኮሱ አዳዲስ የሚሳዔል ጥቃቶችን ማክሸፏንና በቤሩት እንዲሁም በቴህራን ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን መሰንዘሯን ገልጻለች።
ሀና ሰይፉ
መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
