ትራምፕ አገራት ሆርሙዝን ለመክፈት በሚጥሩበት ወቅት ተጨማሪ የኢራን መሰረተ ልማቶችን ኢላማ እንደሚያደርጉ ዛቱ

የአሜሪካ እየተባባሰ የመጣዉ ፉከራ ገበያዎችን እያናጋ ሲሆን፤ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ ለመክፈት በሚጥሩበት ወቅት በኢነርጂ ፍሰት ላይ ያለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ አገራት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አስፈላጊ የሆኑ የኢነርጂ ጭነቶችን እንደገና ለመጀመር መንገዶችን በሚፈልጉበት ወቅት፤ አሜሪካ ‹‹በኢራን ውስጥ የተረፈውን ማውደም ገና አልጀመረችም›› በማለት በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማጠናከር የገቡትን ቃል በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በአሜሪካ እና እስራኤል የአየር ድብደባ ከተጀመረ ወደ አምስት ሳምንታት ያስቆጠረው በኢራን ውስጥ ያለው ጦርነት በክልሉ ውስጥ ውጥረት ማስፈኑንና የፋይናንስ ገበያዎችን ማናጋቱን ቀጥሏል። ይህም ትራምፕ ለግጭቱ ፈጣን መፍትሄ እንዲያገኙ ግፊት እያሳደረባቸው ይገኛል።

የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ውስጥ የተረፈውን ማውደም ገና አልጀመረም ቀጥሎ ድልድዮች ከዚያም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ናቸው” ሲሉ ትራምፕ በማህበራዊ ገጻቸዉ ላይ የጻፉ ሲሆን፤ የኢራን አመራሮች ‹‹ምን መደረግ እንዳለበት ያውቃሉ፤ እናም በፍጥነት መደረግ አለበት!›› ሲሉ አክለዋል።

ቀደም ብሎም አሜሪካ በቴህራን እና በሰሜን ምዕራብ ካራጅ ከተማ መካከል አዲስ የተገነባውን ድልድይ ስትደበድብ የሚያሳይ ቪዲዮ ለጥፈዋል።

‹‹ቢ 1›› የተሰኘው ድልድይ በዚህ ዓመት ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ታቅዶ ነበር።

የኢራን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በአሜሪካ ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲገደሉ 95 ሌሎች ቆስለዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹ያልተጠናቀቁ ድልድዮችን ጨምሮ የሲቪል ተቋማትን መምታት ኢራናውያን እጃቸውን እንዲሰጡ አያስገድዳቸውም››ብለዋል።

ሳራ ዮሐንስ

መጋቢት 25/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *