‹‹የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄዎች በሰፊው ያልተነኩ ናቸው›› – አቶ ፋሲካው ሞላ

የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ የዲሞክራሲና የነፃነት ጉዳዮች ገና ብዙ ስራ እንደሚቀራቸው ገለጹ።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ያሉት በአፋር እና በትግራይ ክልሎች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በመንግስት ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ይፋ ባደረጉት ፕሮጀክት ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄዎች አሁንም በሰፊው ያልተነኩ ናቸው ብለዋል።

አቶ ፋሲካው ባለፉት ዓመታት የተደረጉ ለውጦችን ሲያብራሩ፤ ከመሬት ባለቤትነትና ከብሔር ብሔረሰቦች መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በተወሰነ መልኩ ምላሽ እያገኙ ቢመጡም፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ጉዳዮች ግን ገና ብዙ ስራ እንደሚቀራቸው ጠቁመዋል።

‹‹ከነፃነት፣ ከእኩልነትና ከዲሞክራሲ ጋር በተያያዘ ያለው የህዝብ ጥያቄ ግን ብዙ ያልተነካና ሰፊ ስራ የሚፈልግ ነው››ብለዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውጤታማ እንዲሆን ከውጭ የሚመጡ ሞዴሎችን ብቻ ከመከተል ይልቅ የሀገሪቱን ነባር እሴቶችና ባህሎች መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ ‹‹የዲሞክራሲ እሴቶችና የውይይት ባህሎች ያሏት ሀገር›› መሆኗን የጠቀሱት አቶ ፋሲካው፤‹‹ዲሞክራሲን የግድ ከውጭ አምጥቶ ለመለጠፍ መታገል አያስፈልገንም፤ ይልቁንም የሀገራዊ ሁኔታንና የማህበረሰባችንን ስሪት ግምት ውስጥ ያስገባ ሀገር በቀል የዲሞክራሲ አቀራረብ መከተል ለለውጥ ያፋጥነናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

ከለውጡ በፊት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንዳይሰሩ ተጥሎባቸው የነበረው ገደብ መነሳቱን ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ባለው ምቹ የህግ ማዕቀፍ ተጠቅመው ድርጅቶቹ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በመንግስትና በሲቪል ማህበረሰቡ መካከል የነበረው ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ‹‹ገንቢ ትብብር›› መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ይህንን ትብብር እስከ ወረዳ ድረስ ለማውረድ የቅንጅት መድረኮች መዋቀራቸውንና ባለስልጣኑ ለድርጅቶቹ ድጋፍ ለማድረግ ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስአለም አበበ

ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *