ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 24 ቢሊዮን የዲጂታል ክፍያ ዝውውሮች መከናወናቸውን አስታወቀ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 24 ቢሊዮን የሚጠጉ የዲጂታል ክፍያ ዝውውሮች መከናወናቸውንና የአገሪቱ የፋይናንስ ተደራሽነት 64 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

ባንኩ እ.ኤ.አ በ2025 ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም ሆኖ ለመደራጀትና የገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመንን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ገልጿል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው የሁዋዌ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አማካሪ ዶክተር ናኦል አዲሱ እንደገለጹት፣ አገሪቱ በፋይናንስ ዲጂታላይዜሽን ረገድ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የኔትወርክና የኢንተርኔት ትስስር 70 በመቶ መድረሱ ለዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመላክተዋል።

አማካሪው በንግግራቸው፣ ባንኩ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ውስጥ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የፋይናንስ መረጋጋትን ማረጋገጥና የካፒታል ገበያን ማሳለጥ ዋነኛ ግቦቹ አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎቶችና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች የሪፎርሙ ዋነኛ አካል መሆናቸው ተገልጿል።

ከቴክኖሎጂ እድገቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሳይበር ጥቃትና የፋይናንስ ማጭበርበር ስጋቶችን ለመከላከል፣ ባንኩ የሸማቾች ጥበቃ መመሪያዎችን እያዘጋጀ መሆኑም በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

ይህም የኅብረተሰቡን አመኔታ በማሳደግ የፋይናንስ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋት እንደሚያግዝ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት፣ ብሔራዊ ባንክ ዘመናዊና አስተማማኝ የፋይናንስ መሠረተ ልማት የመገንባት ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አማካሪው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ልዑል ወልዴ

ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *