ጣሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ እንደማይቀየር አስታወቀች


 
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ባለፈው ሳምንት በፈረንሳይ ከተካሄደው  የቡድን 7 ጉባኤ ማጠቃለያ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት አወዛጋቢ አስተያየት “መደነቃቸውን” ገልጸው ሆኖም ይህ ክስተት የሮምን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደማይቀይረው አስታውቀዋል።

አንሳ የተባለው የዜና ወኪል ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ መሠረት፥ሜሎኒ በጉባኤው ወቅት ከእሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሳት “ለምናኛለች” ሲሉ ትራምፕ ባደረጉት እና እሳቸው ቀደም ሲል አጥብቀው ባስተባበሉት የይገባኛል ጥያቄ ዙሪያ ለቀረቡት ሪፖርቶች ምላሽ ሰጥተዋል።

ሜሎኒ በትራምፕ ንግግር ዙሪያ ሲናገሩ “በእውነት በቅንነት ነው የተገረምኩት፤ ይህንን ስናገርም እጅግ እውነተኛ ሆኜ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ሜሎኒ ከዚህ ኩነት ጋር ተያይዞ በኢንተርኔት ላይ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ቪዲዮዎችን ጨምሮ የወጡ  ዘገባዎችንና የተደረጉ ውይይቶችን መከታተላቸውን ገልጸዋል።

“የእኔን አቋም ቁርጠኛ አድርገው ከሚያሳዩ እና በቫይራል ከተሰራጩ ቪዲዮዎች ጀምሮ የተለያዩ ሪፖርቶችን አንብቤያለሁ፥ይሁን እንጂ ሪፖርቶቹ ኔቶ ውስጥ ያሉ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በኢራን ጉዳይ ላይ በነበሩት የድርድር ሂደቶች ላይ ከታየው መሻሻል ትኩረትን ለመቀየር የታለመ ይመስላል” ብለዋል።

አክለውም “በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገውን ክርክር ወደፊት ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌለኝ ቀደም ሲል ገልጫለሁ፣ አሁንም እደግመዋለሁ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ምንም እንኳን ይህ ውዝግብ ቢኖርም የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይለወጥ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“ያም ሆነ ይህ ሃሳቤን አልቀይርም የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላለፉት 80 ዓመታት እንደነበረው ይቆያል፤ በምዕራባውያን ጥንካሬ መሠረት የሆነውን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ማስቀጠል ቀዳሚ ተግባራችን ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

ሀና ሰይፉ

ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *