የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የደላሎችን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ገለጸ
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አምቦ መቃሳ እንደገለፁት በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የሚንቀሳቀሱ ህገ-ወጥ ደላሎችን ለመከላከል የአገልግሎት አሰጣጡን ወደ ዲጂታል አሰራር ሙሉ በሙሉ እያሸጋገሩ መሆኑን አስታዉቀዋል።
ይሁን እንጂ መሥሪያ ቤቱ ለማንም የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ ውክልና እንዳልሰጠም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውን መንገዶች በተመለከተ፣ ፓስፖርትም ሆነ ሌሎች የቪዛ አገልግሎቶች የተገልጋዩን ባዮሜትሪክስ (የጣት አሻራና የአይን ምስል) የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በሦስተኛ ወገን ወይም በደላላ በኩል ጉዳይ ማስፈጸም ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የሙስናና የብልሹ አሰራርን ለመከላከል የገንዘብ ክፍያ ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆን ተደርጓል በአሁኑ ወቅት መሥሪያ ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች 90 በመቶ የሚሆኑት በዲጂታል ፕላትፎርም ላይ የተመሰረቱ ናቸው ብለዋል።
ይህም ተገልጋዮች ከቤታቸው ሆነው ቀጠሮ እንዲይዙና አስፈላጊ ሰነዶችን እንዲልኩ በማድረግ ረጅም ሰልፍና እንግልትን ለማስቀረት አስችሏል።
የድረ-ገጽ መቆራረጥና የኔትወርክ ችግሮችን በተመለከተም፣ መሥሪያ ቤቱ በየጊዜው የማሻሻያ ስራዎችን እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ተገልጋዮች በድረ-ገጽ መጠቀም ቢቸገሩ እንኳ በ28ቱ የክልል ቅርንጫፎች በአካል በመቅረብ አገልግሎቱን በነፃ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 24/ 2018 ዓ.ም
