በአርሲ ዞንና በአካባቢው በብሄር እና በሃይማኖት ስም የሚጠነሰሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የህዝብ ፍላጎት ሳይሆኑ፣ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሰሩ የታጠቁ ሃይሎች ሴራ መሆናቸውን የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ በጅጋ ገለጹ።
ከንቲባው ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ አሰላ የብሄር ብሄረሰቦች አብሮነት ተምሳሌትና “ታናሽ ኢትዮጵያ”ተብላ የምትጠራ ከተማ ናት ብለዋል።
በዚህች ከተማ ውስጥ የማይኖርም ሆነ የማይከበር የህብረተሰብ ክፍል የለም ያሉት ከንቲባው፣ ህዝቡ እርስ በእርሱ የሚጠበቅና የሚደጋገፍ እንጂ የሚጋጭ አለመሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል ነው ያሉት።
አቶ ፀጋዬ አክለውም፣ በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው የሚነሱ የሰላም ስጋቶች ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ መሆናቸውን ጠቁመው፤ “እነዚህ ችግሮች የጥፋት ስብስቦች የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚጠቀሙባቸው ሴራዎች ናቸው” ሲሉ በጽኑ ኮንነዋል።
ህዝቡ ይህንን የጥፋት ሃይሎች ሴራ በመረዳት ለአንድነቱና ለሰላሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ለከተማዋ አስተማማኝ ሰላም መስፈን የነዋሪው አንድነት፣ የመንግስት አስተዳደሩ እና የፀጥታ አካላት በቅንጅት መስራታቸው ያስገኘው ውጤት መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህ የሰላም ድባብ ደግሞ ለከተማዋ የልማት ስራዎች መፋጠን መሰረት ሆኗል ያሉ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 4 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ስራ መጠናቀቁ፣ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ”ቡርቂቱ ፓርክ” እና የወንዞች ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉ፣እንዲሁም ባለሀብቶች በ12 ሄክታር መሬት ላይ ባረፈው የ”አርዱ አይቅ” እና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመላክተዋል።
አሰላ የአትሌቲክስ እና የባለሙያዎች ምንጭነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል የሰላም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ከንቲባው፣ህዝቡ ለሰላሙ ዘብ በመቆም የሴረኞችን መንገድ መዝጋቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ልዑል ወልዴ
ሐምሌ 24/ 2018 ዓ.ም
