በዩክሬን ኪቭ ክልል በሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት የ14 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 27 መቁሰላቸው ተገለፀ

የቅርብ ጊዜው ጥቃት የተፈጸመው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሩሲያ እና በዩክሬን ቢያንስ 27 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።

የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭን ባካበበው ክልል ላይ የተሰነዘረው የሩሲያ ባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ቢያንስ 14 ሰዎችን መግደሉን እና ሌሎችን 27 ማቁሰሉን የከተማዋ ወታደራዊ አስተዳደር አስታውቋል።

ማለዳ ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዩክሬን እና በሩሲያ በተለያዩ ጥቃቶች ቢያንስ 27 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የመጡ ሲሆን፥ የአምስት ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ግጭት የመቀዝቀዝ ምልክት አያሳይም ተብሏል።

የኪቭ ወታደራዊ አስተዳደር ከእኩለ ሌሊት በኋላ በጀመረው ጥቃት ሰባት ቦታዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል።

የከተማዋ ከንቲባ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ‹‹አሁንም በፍርስራሹ ስር ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የፍለጋ እና የማዳን ስራዎች እየተከናወኑ ነው››ሲሉ ፅፈዋል።

ዩክሬን ከቅርብ ወራት ወዲህ የአየር ክልሏን ከሩሲያ ባሊስቲክ ጥቃቶች ለመጠበቅ የአሜሪካ ሰራሽ የፓትሪዮት ሚሳኤል መጥለፊያዎችን ተጨማሪ አቅርቦት እንዲሰጧት አጋሮቿን ስትማጸን ቆይታለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የባሊስቲክ ሚሳኤል መጥለፊያ እጥረት ‹‹ሩሲያ የሰውን ህይወት የሚቀጥፉ መሰል ጥቃቶችን እንድትሰነዝር ያበረታታታል›› ብለዋል።

ዘለንስኪ ባለፈው ማክሰኞ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ አላማዉም በከፊል ዋሽንግተንን የፓትሪዮት ሚሳኤሎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ፈቃድ እንድትሰጥ ለመጠየቅ ነበር።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች ሩሲያ በየካቲት 2022 ጎረቤቷ ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከፈጸመችበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የሲቪል ተጎጂዎች ቁጥር መጨመር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሳራ ዮሐንስ

ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *